2 Chronicles 11

1ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም እንዲመልሱ ከይሁዳና ከብንያም ቤት አንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ወታደሮች ሰበሰበ።

2ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፤ 3“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና በይሁዳና በብንያም ላሉ እስራኤላውያን ሁሉ እንዲህ በል፤ 4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ስለሆነ፣ ወንድሞቻችሁን ለመውጋት ወደዚያ አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ወደየቤታችሁ ሂዱ’ ” አላቸው። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በኢዮርብዓም ላይ መዝመቱን ትተው ተመለሱ።

ሮብዓም የይሁዳን ከተሞች መሸገ

5ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም በማድረግ ለመከላከያ የሚሆኑ ከተሞችን በይሁዳ ሠራ፤ እነዚህም 6ቤተ ልሔም፣ ኤጣም፣ ቴቁሔ፣ 7ቤትጹር፣ ሦኮ፣ ዓዶላም፣ 8ጌት፣ መሪሳ፣ ዚፍ፣ 9አዶራይም፣ ለኪሶ፣ ዓዜቃ፣ 10ጾርዓ፣ ኤሎን፣ ኬብሮን ናቸው። በይሁዳና በብንያም ውስጥ የተመሸጉት ከተሞች እነዚህ ነበሩ። 11እነዚህንም ምሽጎቻቸውን አጠንክሮ፣ አዛዦችን ሾመባቸው፤ ምግብ፣ ዘይትና የወይን ጠጅ አከማቸባቸው። 12በየከተሞቹም ሁሉ ጋሻና ጦር አከማችቶ ይበልጥ አጠናከራቸው። በዚህ ዐይነት ይሁዳንና ብንያምን የራሱ አደረገ።

13በመላው እስራኤል ያሉት ካህናትና ሌዋውያን ከየክልላቸው ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 14ኢዮርብዓምና ልጆቹ ሌዋውያኑን ከእግዚአብሔር የክህነት አገልግሎት ስላባረሯቸው ሌዋውያኑ ማሰማሪያ ቦታቸውንና ንብረታቸውን ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ 15እርሱም ለየኰረብታው መስገጃ እንዲሁም ለሠራቸው የፍየልና የጥጃ ምስሎች የራሱን ካህናት ሾመ። 16ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ ከልባቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። 17በዚሁ ሁኔታ የዳዊትንና የሰሎሞንን መንገድ በመከተል፣ ለሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምንም ረዱ።

የሮብዓም ቤተ ሰብ

18ሮብዓም መሐላትን አገባ፤ አባቷ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ሲሆን፣ እናቷም አቢካኢል የተባለች፣ የእሴይ የልጅ ልጅ የኤልያብ ልጅ ነበረች። 19እርሷም የዑስ፣ ሰማርያና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20ከዚያም የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያ፣ ዓታይ፣ ዚዛ፣ ሰሎሚት የተባሉትን ወለደችለት። 21ሮብዓም መዓካን ከሌሎቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይልቅ አብልጦ ወደዳት። በአጠቃላይ ዐሥራ ስምንት ሚስትና ስልሣ ቁባት፣ ሃያ ስምንት ወንድና ስድሳ ሴት ልጆች ነበሩት።

22ሮብዓም የመዓካን ልጅ አብያን ሊያነግሠው ስለ ፈለገ ከልዑላን ወንድሞቹ ዐልቆ ዋና አደረገው። 23ከወንዶች ልጆቹም ጥቂቱን በይሁዳና በብንያም አውራጃዎች እንዲሁም በተመሸጉት ከተሞች ስለ ሾማቸው፣ ዘዴኛነቱን አሳይቷል። የሚያስፈልጋቸውን በብዛት ሰጣቸው፤ ብዙ ሚስቶችም አጋባቸው።

Copyright information for AmhNASV